ወደ ዋናው ይዘት ይዝለሉ

ጻድቃን ለምን ይሠቃያሉ፣ ክፉዎችስ ለምን ይበለጽጋሉ? ፍትሕ የት አለ?

Court hammer

በዚህ ዓለም ሰዎች በፍትሐዊነት ሲስተናገዱ ብዙ ጊዜ አናይም። ጻድቃን ሲሠቃዩ ክፉዎች ደግሞ ሲበለጽጉ እናያለን። ይህ ለምን ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፣ እግዚአብሔር ፍትሕ ለተነፈጉ ሰዎች ፍትሕን ይሰጣል።

6 እግዚአብሔር ለተጨቈኑ ሁሉ፣
ቅን ፍርድንና ፍትሕን ይሰጣቸዋል።
( መዝሙር 103:6 )

ነገር ግን እግዚአብሔር ፍትሕን የሚሰጥ ከሆነ፣ በዙሪያችን ይህን ያህል ብዙ ግፍ ለምን እናያለን?

ወደ ኋላ እንመልከት። እርስ በርሳችን በፍትሕ ልንተያይ፣ ልንረዳዳና ፍቅርን ልንዘራ ይገባን ነበር። ይልቁንም እዚሁ በምድር ላይ በእግዚአብሔር ፊት ጭካኔ የተሞላባቸውን ነገሮች አደረግን።

37ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን
ለአጋንንት ሠዉ።
38የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፣
ለከነዓን ጣዖታት የሠዉአቸውን፣
ንጹሕ ደም አፈሰሱ፤
ምድሪቱም በደም ተበከለች።
39በተግባራቸው ረከሱ፤
በድርጊታቸውም አመንዝሮች ሆኑ።
40ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤
ርስቱንም ተጸየፈ።
( መዝሙር 106:37-40 )

በዘመናችንም እንኳ ራሳችንን በቅንነት ለማየት እንፈራለን። ድርጊቶቻችንን ብቻ ሳይሆን ሐሳቦቻችንንና ምኞቶቻችንንም በገለልተኝነት መመዘን ያስፈልገናል። ሌሎች ስለ እኛ የሚሰጡትን ቅን አስተያየት መቀበል በጣም ከባድ ነው። ይልቁንም ጣፋጭ ውሸትን እንመርጣለን።

10እናንተ በፍርድ አደባባይ
የሚገሥጻችሁን ትጠላላችሁ፤ እውነት የሚናገረውንም ትንቃላችሁ።
( አሞጽ 5:10 )

ለብዙ መቶ ዘመናት እኛ ሰዎች እንደ እኛ ያሉትን ሰዎች በፍትሕ አልፈረድንም። አምላካችንም ይህን ችላ ብሎ ሊያልፈው አልቻለም። ኢየሩሳሌም እግዚአብሔር እጅግ የሚወዳቸው ሕዝብ ከተማ ብትሆንም፣ እንደ ሌሎቹ ሁሉ ፍትሕን ተቀበለች። ክፉ ነገሮችን እያደረግን መቀጠልና እግዚአብሔር ለዘላለም ይቅር እንደሚለን መተማመን አንችልም።

1“በኢየሩሳሌም መንገዶች እስኪ ውጡ፤ ወደ ላይ ወደ ታችም ውረዱ፤
ዙሪያውን ተመልከቱ ቃኙ፤
በአደባባይዋም ፈልጉ፤
እውነትን የሚሻና በቅንነት የሚሄድ፣
አንድ ሰው እንኳ ብታገኙ፣
እኔ ይህችን ከተማ እምራታለሁ።
( ኤርምያስ 5:1 )
12ጠላቶችም ሆኑ ወራሪዎች፣
የኢየሩሳሌምን በሮች ጥሰው ይገባሉ ብለው፣
የምድር ነገሥታት፣
ወይም ከዓለም ሕዝብ አንዳቸውም አላመኑም።
13ይህ ግን ከነቢያት ኀጢአት፣
ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኗል፤
በውስጧ፣
የጻድቃንን ደም አፍስሰዋልና።
( ሰቈቃወ 4:12-13 )

በሌሎች ላይ በምንፈጽመው ግፍ፣ እውነትን በመጥላታችን፣ በትዕቢታችንና በኃጢአታችን ምክንያት ራሳችንን ከእግዚአብሔር ለየን፤ ራሳችንንም ከፍትሕ ለየን። እንደ ብርሌ የጠራ ውኃ ካለበት ሐይቅ በፈቃዳችን እየራቅን፣ እየራቅን እንሄዳለን፤ ከዚያም ተጠምተን «ውኃው የት አለ? አላየውም!» ብለን እንጮኻለን። እግዚአብሔር የት አለ? ሊረዳን አይችልም?

1እነሆ፤ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤
ጆሮውም መስማት አልተሳናትም።
2ነገር ግን በደላችሁ
ከአምላካችሁ ለይቷችኋል፤
ኀጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል፤
በዚህም ምክንያት አይሰማም።
3እጆቻችሁ በደም፣
ጣቶቻችሁ በበደል ተነክረዋል፤
ከንፈሮቻችሁ ሐሰትን ተናገሩ፤
ምላሶቻችሁ ክፉ ነገርን አሰሙ።
4ፍትሕን የሚጠራ ማንም የለም፤
ጕዳዩን በቅንነት የሚያቀርብ የለም፤
በከንቱ ነገር ታመኑ፤ ሐሰትን ተናገሩ፤
ሁከትን ፀነሱ፤ ክፋትንም ወለዱ።
5የእባብ ዕንቍላል ታቀፉ፤
የሸረሪት ድር ዐደሩ፤
ዕንቍላሎቻቸውን የሚበላ ሁሉ ይሞታል፤
አንዱ በተሰበረ ጊዜም እፉኝት ይወጣል።
6ድሮቻቸው ልብስ አይሆኑም፤
በሚሠሩትም ሰውነታቸውን መሸፈን አይችሉም፤
ሥራቸው ክፉ ነው፤
እጃቸውም በዐመፅ ሥራ የተሞላ ነው።
7እግሮቻቸው ወደ ኀጢአት ይሮጣሉ፤
ንጹሕ ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤
የሚያስቡት ክፉ ሐሳብ ነው፤
በመንገዶቻቸው ጥፋት እና መፍረስ ይገኛሉ።
8የሰላምን መንገድ አያውቁም፤
በጐዳናቸውም ፍትሕ የለም፤
መንገዳቸውን ጠማማ አድርገውታል፤
በዚያም የሚሄድ ሰላም አያገኝም።
9ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቋል፤
ጽድቅም ወደ እኛ አይመጣም፤
ብርሃንን ፈለግን፤ ነገር ግን ሁሉ ጨለማ ነው፤
የብርሃንን ጸዳል ፈለግን፤ የምንሄደው ግን በድንግዝግዝታ ነው።
10በቅጥሩ ላይ እንደ ዕውር ተደናበርን፤
አካሄዳችንም ዐይን እንደሌላቸው በዳበሳ ሆነ፤
ጀንበር በምትጠልቅበት ጊዜ እንደሚሆነው በእኩለ ቀን ተደናበርን፤
በብርቱዎች መካከልም እንደ ሙታን ሆንን።
11ሁላችን እንደ ድቦች እናላዝናለን፤
እንደ ርግቦችም በመቃተት እንጮኻለን፤
ፍትሕን ፈለግን፤ ግን አላገኘንም፤
ትድግናን ፈለግን፤ ነገር ግን ከእኛ ርቋል።
( ኢሳይያስ 59:1-11 )

አዎ፣ ኃጢአት ሠርተናል። አዎ፣ አሁንም ኃጢአት እንሠራለን። ስሕተቶችን ፈጽመናል። ቢሆንም ልባችንን ለእግዚአብሔር መክፈት፣ ንስሐ መግባትና ይቅርታን መለመን እንችላለን። ልባችንን ለእግዚአብሔር ስንከፍት ደግሞ ከአሁን ጀምሮ ለኃጢአት እንዝጋው።

12“አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች እንዲህ በላቸው፤ ‘ጻድቅ ሰው ትእዛዝን በተላለፈ ጊዜ የቀድሞ ጽድቁ አያድነውም፤ ኀጢአተኛ ሰው ከኀጢአቱ ከተመለሰ፣ ከቀድሞ ክፋቱ የተነሣ አይጠፋም። ጻድቅ ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ በቀድሞ ጽድቁ ምክንያት በሕይወት እንዲኖር አይደረግም።’ 13ጻድቁን ሰው በርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ብለው፣ እርሱም ጽድቁን ተማምኖ ክፋት ቢሠራ፣ ከሠራው ጽድቅ አንዱም አይታሰብለትም፤ በኀጢአቱም ምክንያት ይሞታል። 14እንዲሁም ክፉውን ሰው፣ ‘በርግጥ ትሞታለህ’ ብለው፣ እርሱም ከኀጢአቱ ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ፣ 15ለሰጠው ብድር የተቀበለውን መያዣ ቢመልስ፣ የሰረቀውንም መልሶ ቢሰጥ፣ ሕይወት የሚሰጡትን ትእዛዞች ቢከተል፣ ክፉ ነገርንም ባያደርግ፣ በርግጥ እርሱ በሕይወት ይኖራል፤ አይሞትምም። 16ከሠራው ኀጢአት አንዱም አይታሰብበትም፤ ቀናውንና ትክክለኛውን አድርጓልና፤ በርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17“ይህም ሆኖ የአገርህ ሰዎች፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላሉ፤ ቀና ያልሆነው ግን የእነርሱ መንገድ ነው።
( ሕዝቅኤል 33:12-17 )

እግዚአብሔር እንደሚሰማን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከኃጢአታችን ለመመለስ፣ ይቅርታን ለማግኘትና የእግዚአብሔርን ጸጋ ለመቀበል መቼም ቢሆን እንደማይረፍድ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

13አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣
እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል።
( መዝሙር 103:13 )
19 እኔ የምወድዳቸውን እገሥጻለሁ፤ እቀጣለሁም። ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ።
( ራእይ 3:19 )

ያለ ጥርጥርም ፍትሕ ያሸንፋል፤ እያንዳንዱም የሚገባውን ይቀበላል።

10“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣
እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣
ልብን እመረምራለሁ፤
የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።”
( ኤርምያስ 17:10 )

ታዲያ በእውነት ጻድቃን የሆኑት ለምን ይሠቃያሉ?

በምድር ላይ ኃጢአት የሌለበት አንድም ሰው አለመኖሩን ብንረሳ እንኳ፣ የእግዚአብሔርን መንገዶች ሁልጊዜ መረዳት እንደማንችል ማስታወስ ያስፈልገናል። ምንም እንኳ መልካምና ክፉ ምን እንደሆነልንረዳ ብንችልም፣ ሙሉውን ሥዕል ስለማናይ ያንን እውቀት በትክክል ልንጠቀምበት አንችልም።

9“ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣
መንገዴ ከመንገዳችሁ፣
ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።
( ኢሳይያስ 55:9 )

የምናውቃቸው መልካም ሰዎች በሕይወታቸው ይህን ያህል ብዙ ሐዘን ለምን እንደሚደርስባቸውም ሁልጊዜ አንረዳም። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መከራ ስለ ተቀበሉ ሰዎች አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። ከባርነት ተነሥቶ በግብፅ ሁለተኛው ኃያል ሰው እስከ መሆን ስለ ደረሰው ስለ ዮሴፍ የሚናገረውን ታሪክ ታስታውሱ ይሆናል።

17በባርነት የተሸጠውን ሰው፣
ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ።
18እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤
በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ።
19የተናገረው ቃል እስኪፈጸምለት፣
የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው።
( መዝሙር 105:17-19 )

ዮሴፍ ሲጠብቀው የነበረውን በረከት ከመቀበሉ በፊት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አለፈ። የደረሱበትም ፈተናዎች የግድ ለኃጢአቱ ቅጣት አልነበሩም፤ ይልቁንም ሊቀበለው ላለው ከፍተኛ ሥልጣን ብቁ ያደረገው አስፈላጊ የትምህርት ሂደት ነበሩ።

ኢየሱስ ራሱ ምንም ኃጢአት ባይሠራም በምድራዊ ሕይወቱ መከራን ተቀበለ።

8የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤
( ዕብራውያን 5:8 )

አንዳንዶቻችን ወላጆቻችንን ወይም የምንወዳቸውን ሰዎች አጥተናል። ሕይወታቸውን እንዲያተርፍልን ቀንና ሌሊት ወደ እግዚአብሔር ብንጸልይም ሞቱ። እግዚአብሔር ለምን አይሰማንም?

የምንወዳቸው ሰዎች ሲሞቱ ከእነርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ይቋረጣል፤ ከእንግዲህ ልናያቸው፣ ልናነጋግራቸው፣ ፈገግታቸውን ልናይ ወይም የሚያበረታታ ምክር ልንቀበል አንችልም። ሞታቸውን ምንም ልናደርግ የማንችልበት ፍጻሜ አድርገን እናየዋለን… እግዚአብሔር ግን ይችላል። ለእግዚአብሔር አንድም ሰው የሞተ አይደለም። እግዚአብሔር እኛንም ጸሎታችንንም ይሰማል። እርሱ ለእኛ መልካምን ይሻል፤ ላጣናቸውም ሰዎች ደግሞ መልካምን ይሻል።

1ጻድቅ ይሞታል፤
ይህን ግን ማንም ልብ አይልም፤
ለእግዚአብሔር ያደሩ ሰዎች ይወሰዳሉ፤
ጻድቃን ከክፉ ይድኑ ዘንድ፣
መወሰዳቸውን፣
ማንም አያስተውልም።
2በቅንነት የሚሄዱ፣
ሰላም ይሆንላቸዋል፤
መኝታቸው ላይ ያርፋሉ።
( ኢሳይያስ 57:1-2 )

ለእግዚአብሔር ታማኝ እንደሆንህ ታምናለህ፣ ነገር ግን ሕይወት በጣም ከብዶብሃል? አምላካችን እንደ አፍቃሪ አባት ያስተምረናል፣ ይገሥጸናል፣ ያነጻናል፣ ከእግዚአብሔር የሚመጣውንም ስጦታ ለመቀበል ያዘጋጀናል።

7እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ይዟችኋልና የተግሣጽን ምክር ታገሡ፤ ለመሆኑ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? 8ልጆች ሁሉ በሚቀጡበት ቅጣት ተካፋይ ካልሆናችሁ፣ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። 9ከዚህም በላይ፣ እኛ ሁላችን የሚቀጡን ምድራዊ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር። ታዲያ ለመናፍስት አባት እንዴት አብልጠን በመገዛት በሕይወት አንኖርም! 10አባቶቻችን መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል። 11ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል።
( ዕብራውያን 12:7-11 )
6አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። 7እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ፣ እውነተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው።
( 1 ጴጥሮስ 1:6-7 )

ክፉ አድራጊዎች ሰላማዊ ሕይወት ሲኖሩ፣ ከፍትሕ ሲያመልጡና በብዙ ተድላ ሲደሰቱ እናያለን። አንዳንዶቹ ሕይወታችንን አፍርሰዋል፤ ፍላጎታቸውን ለማርካት ሌሎችን መጠቀምም ያስደስታቸዋል። በእነርሱ ላይ የተፈጸመ አንዳች ፍርድ አናይም። ቢሆንም ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያመልጡ እንደሚችሉ ማሰብ የለብንም።

4አንዳች ጣር የለባቸውም፤
ሰውነታቸውም ጤናማና የተደላደለ ነው።
5በሰዎች የሚደርሰው ጣጣ አይደርስባቸውም፤
እንደ ማንኛውም ሰው መከራ አያገኛቸውም።
6ስለዚህ ትዕቢት የዐንገት ጌጣቸው ነው፤
ዐመፅንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈዋል።
7የሠባ ዐይናቸው ይጕረጠረጣል፤73፥7 የዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ የሱርስቱና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን፣ ከደነደነው ልባቸው በደል ይወጣል ይላል።
ልባቸውም በከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይፈስሳል።
8በፌዝና በክፋት ይናገራሉ፤
ቀና ቀና ብለውም በዐመፅ ይዝታሉ።
9አፋቸውን በሰማይ ላይ ያላቅቃሉ፤
አንደበታቸውም ምድርን ያካልላል።
10ስለዚህ ሕዝቡ ወደ እነርሱ ይነጕዳል፤
ውሃቸውንም በገፍ73፥10 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ይጠጣሉ።
11“ለመሆኑ እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል?
በልዑልስ ዘንድ ዕውቀት አለ?” ይላሉ።
( መዝሙር 73:4-11 )
18በርግጥ በሚያዳልጥ ስፍራ አስቀመጥሃቸው፤
ወደ ጥፋትም አወረድሃቸው።
19እንዴት ፈጥነው በቅጽበት ጠፉ!
በድንጋጤ ፈጽመው ወደሙ።
20ሰው ከሕልሙ ሲነቃ እንደሚሆነው፣
ጌታ ሆይ፤ አንተም በምትነሣበት ጊዜ፣
እንደ ቅዠት ከንቱ ታደርጋቸዋለህ።
( መዝሙር 73:18-20 )
6ደነዝ ሰው ይህን አያውቅም፤
ሞኝም አያስተውለውም።
7ክፉዎች እንደ ሣር ቢበቅሉ፣
ክፉ አድራጊዎች ቢለመልሙ፣
ለዘላለሙ ይጠፋሉ።
( መዝሙር 92:6-7 )
19በጨካኞች ድርጊት አትጨነቅ፤
በክፉዎችም አትቅና፤
20ግፈኛ ተስፋ የለውምና፤
የክፉዎችም መብራት ድርግም ብላ ትጠፋለች።
( ምሳሌ 24:19-20 )

እግዚአብሔር ሁልጊዜ ትክክለኛና ፍትሐዊ መሆኑን አስታውሱ። መንገዶቹን ሁልጊዜ አንረዳም፤ አንዳንድ ጊዜም በሌሎች ላይ ለመፍረድ እንቸኩላለን። ይልቁንም ፍርድን ለእግዚአብሔር እንተው፤ በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ በአክብሮትና በፍቅርለመያዝ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።

18 እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣
በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።
19ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤
ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም።
( መዝሙር 145:18-19 )
8እግዚአብሔር ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋራ ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።”
( ዘዳግም 31:8 )
አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)